በጋምቤላ ክልል የሙያ ብቃት ምዘና ፈተና ኮምፒተራይዝድ መሆኑ ቀደም ሲል የነበሩትን ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችል ነው ሲሉ የክልሉ የሙያ ምዘና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አኳታ ኡሚዩ ገለጹ፡፡ኤጀንሲው በዘንድሮ አመት በተለያየ የሙያ መስክ የሰለጠኑ ከሁለት ሺ ሦስት መቶ በላይ ተፈታኞች የብቃት ምዘና መውሰዳቸውም ተመልክቷል፡፡ከጋምቤላ ፕረስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት (ሰኔ 11/2013)የክልሉ የሙያ ብቃት ምዘና ኤጀንሲ ዳይሬክተር ወ/ሮ አኳታ ኡሚዩ እንደገለጹት ቀደም ሲል ለተፈታኞች ፈተናው የሚሰጠው በወረቀት መሆኑን ገልጸው አሁን ግን በኮምተራይዝድ መሆኑ የተፈታኞችን ቅሬታ ከመመለስ በተጨማሪ ጊዜን ለመቆጠብና ጥራት ያለው ስራ ለመስራት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡ዳይሬክተሯ አክለውም ፈተናው በኮምፒውተር መሰጠቱ ኩረጃንና የሃሰት የምዘና የምስክር ወረቀቶችን ለማስቀረት ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ስልጠናውን ሰልጥነው የሚወጡ ሰልጣኞች ወደ ምዘና ፈተና በሚገቡበት ጊዜ ውጤታቸውን ከሚጠበቀው በታች የወረደ መሆኑን ገልጸው ስልጠና የሚሰጡት ተቋማቶች ላይ ቁጥጥርና ጥብቅ የሆነ አስራር ሊኖረው እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡በመጨረሻም አርሶ አደሮች ምርታቸውን ወደ ገበያ አወዳድረው ለመሸጥ የሚረዳቸውን የምስክር ወረቀት ለማግኘት ወደ ኤጀንሲው በመምጣት መመዘን እንደሚችሉ ጠቅሰዋል፡፡ የኤጀንሲው የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተስፋዬ ሰጠኝ በበኩላቸው ምዘናው 2007 ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በ36 የሙያ ዘርፍ ከ25,000 በላይ የሚሆኑ ተፈታኞች መመዘናቸውን ተናግረዋል፡፡አያይዘውም መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማቶች ሰልጠነው ለሚወጡ ሰልጣኞች የብቃት ምዘናው ቢሰጥም ተፈታኞቹ የሚያመጡት ውጤት አጥጋቢ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡